Ethical Officer

በአብክመ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በማዕ/ጎን/ዞን አስተዳደር የአለፋ ወረዳ አስተዳደር የሥነ-ምግባር መኮነን

ራዕይ፡-

  • በወረዳው በ2025 ሙስና ለልማትና ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ ደርሶ ማየት

ተልዕኮ

  • በወረዳውየሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርትን በማስፋፋት የሙስና ወንጀልንና ብልሹ አሰራርን በመከላከል፣ በመመርመር እና ሙሰኞችን ለፍርድ አቅርቦ እንዲታረሙ በማድረግ ከሙስና ነፃ የሆነ ህ/ሰብ መገንባት ነው፡፡

ዓላማ

  • በወረዳው ባሉ መምሪያዎች የፀረ-ሙስና ትምህርትን በመጠቀም ሰራተኛውን በሥራ ዲስኘሊን፣ በሙያ ሥነ-ምግባር፣ በህዝብ አገልጋይነትና በኃላፊነት ስሜት በማነጽ የነቃና ሙስናን ሊሸከም የማይችል ማህበረሰብ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ማድረግ፣
  • በበወረዳው ባሉ ተቋማት ሙስናንና ብልሹ አሰራርን መከላከል
  • በወረዳ የፀረ-ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ ህዝባዊ መሠረት ይኖረው ዘንድ መረባረብ
  • የሙስና ወንጀሎችና ብልሹ አሰራሮች እንዲጋለጡና በወቅቱ ቀርበው እንዲመረመሩ በአጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ጥረት ማድረግ፡፡

በአብክመ ሥነ-ምግባር ፀረ ሙስና ኮሚሽን

 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር የአለፋ ወረዳ አስተዳደር የስነ ምግባር መኮንን ተግባርና ኃላፊነት

  1. የተቋሙ የበላይ አመራርና ሠራተኞች በስነ-ምግባርና በጸረ-ሙስና ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ ይዳብር ዘንድ ተገቢውን ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል፤
  2. በተቋሙ ውስጥ ሙስናንና ስነ-ምግባርን የሚመለከቱ ህግጋት፣ ደንቦችና መመሪያዎች መከበራቸውን በቅርብ ይከታተላል፣ ስለአፈጻጸማቸው የበላይ ሃላፊውን ያማክራል፤
  3. ከየደረጃው የስራ ሃሊፊዎች፣ ሰራተኞችና አግባብነት ካለቸው ክፍሎች ጋር በመተባበር ረቂቅ የስነ-ምግባር መመሪያ ያዘጋጃል፣ ለበላይ አመራሩ አቅርቦ ያስጸድቃል፣ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤
  4. ከተቋሙ የበላይ ሃላፊ ጋር በመመካከር የሙስናና የብልሹ ስነ-ምግባር በር የሚከፍቱ አሰራሮች ተለይተው ይጠኑ ዘንዴ የኮሚሽኑ ሃሳብ ያቀርባል፣ የጥናቱን ውጤት ተንተርሰው የሚሰነዘሩ ምክረ-ሃሳቦች ቢኖሩ ተግባራዊ መደረጋቸውን ይከታተላል፤
  5. በተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአት እንዲሻሻሉ የበላይ ሃላፊውን ያማክራል፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ አድልዎ እንዳይፈጸም ይከታተላል፣ ይኸው ተፈጽሞ ሲገኝም ለበላይ ሃላፊው ያሳውቃል፤
  6. በተቋሙ ውስጥ ስነ-ምግባር እንዲዳብር፣ የሃሊፊነት ስሜት እንዱጎለብትና የጸረ-ሙስና ትግል ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ የሚያግዙ የስነ-ምግባር አውታሮች ይቋቋሙ ዘንድ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፤
  7. ተቋሙ ከሚያከናውናቸው ተግባራትና ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ የስነ-ምግባር ጥሰቶችን የሚያመላክቱ ጥቆማዎችን ይቀበላል፣ በተቋሙ የስነ-ምግባር ደንብና መመሪያ መሰረት እነዚን ጥቆማዎች በማጣራት አስፈሊጊው እርምጃ እንዲወሰድ ተገቢውን የውሳኔ ሃሳብ አዘጋጅቶ ለበላይ ሃላፊው በወቅቱ ያቀርባል፣ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፣ ስለ አፈጻጸሙ ለኮሚሽኑ ዘገባዎችን ያቀርባል፤
  8. በተቋሙ ውስጥ የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው ወይም ከሌሎች ወገኖች የቀረቡ ጥቆማዎች ሲኖሩ ይህንኑ ለኮሚሽኑ ወይም አግባብ ላለው ሌላ   የስልጣን አካል ሪፖርት ያደርጋል፣ ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ ይከታተላል፤
  9. የሰራተኛ ቅጥርን፣ የደረጃ እድገትን፣ ዝውውርን፣ ስልጠናንና የመሳሰለትን አስመልክቶ በተቋሙ  ውስጥ የስነ-ምግባር ደንብ ወይም መመሪያ ተጥሷል ብሎ ሲያምን ወይም ስለዚሁ ጥቆማ ሲደርሰው ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ይህንኑ ቅሬታ ከአስተያየት ጋር ለበላይ ሃላፊው ወይም አግባብ ላለው ሌላ አካል ያሳውቃል፣ ተግባራዊነቱንም ይከታተላል፤
  10. የእቃ፣ የግንባታ ወይም የአገልግሎት ግዥን ወይም ከዚሁ ጋር የተያያዘን ጨረታ ወይም ማናቸውንም አይነት ሌላ ውል በሚመለከት ደንብና መመሪያ ተጥሷል ብሎ ሲያምን ወይም ስለዚሁ ጥቆማ ሲደርሰው ከበላይ ሃላፊው ጋር በመነጋገር ለኮሚሽኑ አሳውቆ የተጀመረው እንቅስቃሴ ለጊዜው እንዲታገድና እንዲጣራ ያስደርጋል፣ ሆኖም የበላይ ሃላፊው ራሱ በድርጊቱ ተሳታፊ ስለመሆኑ መረጃ ካለው ጉዳዩን በቀጥታ ለኮሚሽኑ ያስተላልፋል፤
  11. ሰራተኛው ሙስናና ብሌሹ አሰራርን ወይም የስነ-ምግባር ጥሰቶችን በማጋለጡ ሳቢያ ማናቸውም አይነት ተጽእኖ እንዲይደርስበት ክትትል ያደርጋል፣ ተጽእኖ ያደረሰበት ካለም ድርጊቱን እያጣራ ከተጨባጭ ማስረጃ ጋር ለበላይ  ሃላፊው ሪፖርት ያደርጋል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፤ ሆኖም ተጽእኖ አድራጊው ራሱ የተቋሙ ሃላፊ በሆነ ጊዜ ጉዳዩን በቀጥታ ለኮሚሽኑ  ያሳውቃል፤
  12. የተቋሙ ሰራተኞች በሙስናና በስነ-ምግባር ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ ውይይቶች እንዲያካሂዱ የበላይ ሃላፊውን ያማክራል፣ ያነቃቃል፤
  13. በራሱም ሆነ በውስጥ ወይም በውጭ ኦዲተሮች ወይም በህዝብ ቅሬታ ሰሚና በዲሲፕልን ኮሚቴዎች አሳሳቢነት ተገቢው አስተዳደራዊ  እርምጃ እንዲወሰድባቸው ወይም እንዲታረሙ ሪፖርት በቀረበባቸው ሰራተኞች ላይ ክትትል በማድረግ ውጤቱን ለበላይ  ሃላፊው ያሳውቃል፣ ይኸው ለተቋሙ ወይም ለድርጅቱ ተቆጣጣሪ አካልና ለኮሚሽኑ ጭምር በግልባጭ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡
  14. ህጋዊ መስፈርቶችን ተጠቅሞ በተቋሙ ወይም በድርጅቱ ውስጥ ሙስናን ወይም ብልሹ አሰራሮችን በመዋጋት ግንባር ቀደም የሆኑና አርአያነት ያላቸውን ሰራተኞችና የስራ ሃሊፊዎች ዝርዝር መዝግቦ ይይዛል፣ ሲጠየቅም የበላይ ኃላፊውን በቅድሚያ እያሳወቀ መረጃውን ለኮሚሽኑ ይሰጣል፤
  15. በተቋሙ ውስጥ ስነ-ምግባርን በማስፈንና ሙስናንም ሆነ ብልሹ አሰራሮችን በመዋጋት ረገድ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ያስተባብራል፤
  16. በህግ መሰረት ሃብትና ንብረታቸውን የማስመዝገብ ግዴታ ያለባቸውን የመንግስት ተሿሚዎች፣ የህዝብ ተመራጮችና ሰራተኞች መረጃ ይሰበስባል፣ አደራጅቶ ይይዛል፣ ሃብት ማስመዝገባቸውን ይከታተላል፣ ከኮሚሽኑ በሚሰጠው ውክልና መሰረት ሃብት ይመዘግባል፣ ይህንኑ በ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ ለኮሚሽኑ ያስተላልፋል፤
  17. በክፍሉ ስለተከናወኑ ተግባራት፣ ስላጋጠሙ ችግሮችና ስለተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ወቅታዊ ሪፖርቶችን እያዘጋጀ ለተቋሙ የበላይ ሃላፊ ያቀርባል፣ ይህንኑ በግልባጭ ለኮሚሽኑ ያሳውቃል፤
  18. አግባብ ባለው ህግ መሰረት ተለይተው የሚሰጡትን ሌሎች ስነ-ምግባር ነክ ተግባራት ያከናውናል፡፡

የተቋሙ ሠራተኞች ኃላፊነት

  1. ማንኛውም የተቋሙ ሠራተኛ የሥነ-ምግባር መኮንኑ ለሥራው ባስፈለገው መጠን የሚጠይቃቸውን ማናቸውንም መረጃዎችና ሌሎች ድጋፎች በመስጠት ረገድ የመተባበር ግዴታ አለበት፣
  2. በሌሎች ሕጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የሥነ-ምግባር መኮንን የሚጠይቀውን ተፈላጊ የስራ ትብብር መከልከል አስተዳደራዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡

በአብክመ የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር  የስነ-ምግባር መኮነን የተዘጋጀ

ስልክ ቁጥር

        058-111-0923

         ፖስታ 154

ታህሣሥ 2011

በአብክመ የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የማዕ/ጎን/ዞን አስተዳደር በስነ-ምግባር መኮነን ስለጥቆማ አቀራረብ  

ጠቋሚ ማን ነው?

ማንኛውንም የሙስና ድርጊት፣ ከባድ የስነ-ምግባር መጣስንና ብልሹ አሰራርን የተመለከተ መረጃ የሚሰጥ ሰው ወይም ድርጅት ማለት ነው፡፡

ጠቋሚው የሚጠቁመው ምንድን ነው?

ጠቋሚው የሚጠቁመው ማንኛውንም የተፈፀመ ወይም ሊፈፀም የታቀደ ሙስናን፣ ከባድ የስነ-ምግባር መጣስን እና ለሙስና ሊያጋልጥ የሚችል አሰራር ነው ተብሎ ሲታሰብ ስም ተገልፆ ወይም ሳይገለጽ በተለያዩ ዘዴዎች መጠቆም የሚቻል ሲሆን ስልጣን ላለው አካል ወይም ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ ጥቆማዎች ለማቅረብ ለሚፈልጉ ጥቆማ አቅራቢዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን መረጃ በተቻለ መጠን አደራጅተው ቢያቀርቡ ለኮሚሽኑ ወይም ስልጣን ላለው አካል አሰራር አመች ይሆናል፡፡

 የሚቀርበው ጥቆማ፡-

  • የጠቋሚ ስምና አድራሻ፣
  • የተፈፀመው ድርጊት ምን እንደሆነ፣
  • ድርጊቱን ፈፀመ የተባለውን ተጠርጣሪ ማንነት ስም፣ ሙያ ወይም ስራ፣ አድራሻ፣ እድሜና የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ የስራ መደቡ፣
  • ድርጊቱ የተፈፀመበት መ/ቤት፣
  • ድርጊቱ ተፈፀመ የተባለበት ቦታና ጊዜ፣
  • በድርጊቱ የተጠቀሙ ወይም የተጎዱ ሰዎች፣
  • በገንዘብ ሊገመት የሚችል ከሆነ፣ በድርጊቱ የተገኘ ጥቅም መጠን ወይም የደረሰ ጉዳት ግምት ወይም ከድርጊቱ መፈፀም ጋር በተያያዘ የተደረገ ውል፣ ብድር፣ ቀረጥ፣ ወዘተ ገንዘብ መጠን፣
  • የጉዳዩን እውነትነት ሊያስረዱ የሚችሉ ማስረጃዎች የሚገኙበት ቦታ ወይም ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ወይም ምስክሮች ስምና አድራሻ እንዲሁም፣
  • ጉዳዩን በተመለከተ ተጀምሮ ያለምርመራ መኖሩንና ያለመኖሩን ወይም በጉዳዩ ላይ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ክርክር እየተደረገበት ወይም ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡
  • ከዚህ በተጨማሪ ጠቋሚዎች የሰጡትን መረጃ በራሳቸው እጅ ጹሁፍ ጽፈው እንዲፈርሙ ይህ ካልሆነ ደግሞ ስልጣን ላለው አካል ወይም ለኮሚሽኑ ባለሙያ በቃል የሰጡትን ዝርዝር መረጃ ተነቦላቸው ትክክለኛነቱን አረጋግጠው ፊርማቸውን እንዲያስቀምጡ ስልጣን ያለው አካል እንዲሁም ኮሚሽኑ ትብብራቸውን የሚጠይቅ መሆኑ፡፡
  • ይህ ካልሆነ ጠቋሚዎች መረጃቸውን በጹሁፍ ለማቅረብ የማይቻል ከሆነ ጥቆማቸውን ስልጣን ላለው አካል ወይም ለኮሚሽኑ ባለሙያ በዝርዝር ካቀረቡ በኋላ ቢቻል ያቀረቡት መረጃ ተነቦላቸውና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው እንዲፈርሙበት የሚጠይቅ መሆኑን መረዳት እንደሚገባቸው፡፡

የሙስና ወንጀል ጥቆማ ለማን ሊቀርብ ይችላል?

  • ስልጣን ላለው አካል ወይም
  • ለኮሚሽኑ

ስልጣን ያለው አካል ወይም ኮሚሽኑ ጥቆማ የሚቀበለው በየትኞቹ ተቋማት ውስጥ ስለተፈፀመ ሙስና ወይም ብልሹ አሰራር ነው?

  • ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመንግስት በጀት በሚተዳደሩ እና በዞን የመንግስት ሰራዎች በሚከናወኑባቸው መ/ቤቶች፣
  • የክልሉ መንግስት ለዞኑ ከሚሰጠው ድጎማ ጋር በተያያዘ በዞን መ/ቤቶች

በህዝባዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን?

  • በወንጀል ህግና በሌሎች ህጎች የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች በመንግስት ባለስልጣኖች ወይም ሠራተኞች በህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ወይም በሌሎች ሰዎች የተፈፀመ እንደሆነ፣
  • ከላይ የተጠቀሱት ቢኖሩም ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ ማለትም ከግንቦት 17/1993 ዓ/ም በፊት በምርመራና በፍርድ ቤት ሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮችን አይመለከትም፡፡

ጠቋሚው ጥቆማውን በምን መንገድ ሊያቀርብ ይችላል?

የሙስና ድርጊት ተፈፀሟል ወይም ሊፈፀም ታቅዷል ተብሎ ሲታሰብ ስም ገልፆ ወይም ሳይገለጽ በአካል በመገኘት፣

  • በጹሁፍ ወይም በቃል፣
  • በፖስታ፣
  • በስልክ፣
  • በፋክስ ወይም በኢሜል እንዲሁም
  • ከስራ ሰዓት ውጪ ቀጠሮ በመያዝ የሚመለከተውን አካል በማናገር ጥቆማውን ማቅረብ የሚቻል ይሆናል፡፡

ከኃላፊነት ነፃ መሆን ማለትስ ምን ማለት ነው?

በህግ፣ በቃለ መሃላ ወይም በስምምነት ማስረጃን በሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ያለበት ማንኛውም ሰው ማስረጃውን አግባብ ላለው አካል በመስጠቱ ህጉን፣ ቃለ መሃላውን ወይም ስምምነቱን እንደጣሰ አያስቆጥረውም፡፡

የጠቋሚዎች ጥበቃ ምን ይመስላል?

አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ለሙስና ወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች የአካልና የስራ ዋስትና ጥበቃ የሚሰጥበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ በህግ በሚወሰን መሰረት ጥበቃ የማድረግ አንድ ስልጣን ያለው አካል ወይም የኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባር እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመጠየፍ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር የበኩላችን ድርሻ ልንወጣ ይገባል፡፡

በአብክመ የስነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር

በስነ-ምግባር መኮነን የተዘጋጀ 

ስልክ ቁጥር 0581110923

     ፖ.ሳ.ቁ 154

Scroll to Top